ኦሪት ዘኍልቍ Orit ZeHwilQwi
Numbers / Bamidbar #8
In Amharic and English

Can’t see Amharic font?

 

ኦሪት ዘኍልቍ 8

Numbers 8

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

1 And the Lord spake unto Moses, saying,

2 መብራቶቹን ስትለኵስ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ ብለህ ለአሮን ንገረው።

2 Speak unto Aaron, and say unto him, When thou lightest the lamps, the seven lamps shall give light over against the candlestick.

3 አሮንም እንዲሁ አደረገ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን ለኰሰ።

3 And Aaron did so; he lighted the lamps thereof over against the candlestick, as the Lord commanded Moses.

4 መቅረዙም እንዲህ ሆኖ ተሠርቶ ነበር ከተቀጠቀጠ ወርቅ ተሠራ እስከ አገዳውና እስከ አበቦቹ ድረስ ከተቀጠቀጠ ሥራ ነበረ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዙን እንዲሁ አደረገ።

4 And this work of the candlestick was of beaten gold, unto the shaft thereof, unto the flowers thereof, was beaten work: according unto the pattern which the Lord had shewed Moses, so he made the candlestick.

5 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

5 And the Lord spake unto Moses, saying,

6 ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው።

6 Take the Levites from among the children of Israel, and cleanse them.

7 ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ሁሉ ምላጭ ያሳልፉ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ይታጠቡም።

7 And thus shalt thou do unto them, to cleanse them: Sprinkle water of purifying upon them, and let them shave all their flesh, and let them wash their clothes, and so make themselves clean.

8 ወይፈንን፥ ለእህሉም ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፥ ሌላውንም ወይፈን ለኃጢአት መሥዋዕት ውሰድ።

8 Then let them take a young bullock with his meat offering, even fine flour mingled with oil, and another young bullock shalt thou take for a sin offering.

9 ሌዋውያንንም በመገናኛው ድንኳን ፊት አቅርብ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ።

9 And thou shalt bring the Levites before the tabernacle of the congregation: and thou shalt gather the whole assembly of the children of Israel together:

10 ሌዋውያንንም በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው የእስራኤልም ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው።

10 And thou shalt bring the Levites before the Lord: and the children of Israel shall put their hands upon the Levites:

11 አሮንም ሌዋውያን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ስጦታ አድርጎ፥ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ።

11 And Aaron shall offer the Levites before the Lord for an offering of the children of Israel, that they may execute the service of the Lord.

12 ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ ለሌዋውያንም ስለ ማስተስረያ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ።

12 And the Levites shall lay their hands upon the heads of the bullocks: and thou shalt offer the one for a sin offering, and the other for a burnt offering, unto the Lord, to make an atonement for the Levites.

13 ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ስጦታ አድርገህ አቅርባቸው።

13 And thou shalt set the Levites before Aaron, and before his sons, and offer them for an offering unto the Lord.

14 እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ።

14 Thus shalt thou separate the Levites from among the children of Israel: and the Levites shall be mine.

15 ከዚያም በኋላ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ ታነጻቸውማለህ፥ ስጦታም አድርገህ ታቀርባቸዋለህ።

15 And after that shall the Levites go in to do the service of the tabernacle of the congregation: and thou shalt cleanse them, and offer them for an offering.

16 እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ማኅፀን በሚከፍት ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ።

16 For they are wholly given unto me from among the children of Israel; instead of such as open every womb, even instead of the firstborn of all the children of Israel, have I taken them unto me.

17 በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው።

17 For all the firstborn of the children of Israel are mine, both man and beast: on the day that I smote every firstborn in the land of Egypt I sanctified them for myself.

18 በእስራኤልም ልጆች በኵራት ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ።

18 And I have taken the Levites for all the firstborn of the children of Israel.

19 የእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደሱ በቀረቡ ጊዜ መቅሠፍት እንዳያገኛቸው፥ ለእስራኤል ልጆች ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአቸዋለሁ።

19 And I have given the Levites as a gift to Aaron and to his sons from among the children of Israel, to do the service of the children of Israel in the tabernacle of the congregation, and to make an atonement for the children of Israel: that there be no plague among the children of Israel, when the children of Israel come nigh unto the sanctuary.

20 ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው።

20 And Moses, and Aaron, and all the congregation of the children of Israel, did to the Levites according unto all that the Lord commanded Moses concerning the Levites, so did the children of Israel unto them.

21 ሌዋውያንም ከኃጢአት ተጣጠቡ፥ ልብሳቸውንም አጠቡ አሮንም ስጦታ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፥ አሮንም ያነጻቸው ዘንድ አስተሰረየላቸው።

21 And the Levites were purified, and they washed their clothes; and Aaron offered them as an offering before the Lord; and Aaron made an atonement for them to cleanse them.

22 ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ይሠሩ ዘንድ ገቡ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው።

22 And after that went the Levites in to do their service in the tabernacle of the congregation before Aaron, and before his sons: as the Lord had commanded Moses concerning the Levites, so did they unto them.

23 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

23 And the Lord spake unto Moses, saying,

24 የሌዋውያን ሕግ ይህ ነው ከሀያ አምስት ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት በመገናኛው ድንኳን ሥራ ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ።

24 This is it that belongeth unto the Levites: from twenty and five years old and upward they shall go in to wait upon the service of the tabernacle of the congregation:

25 ዕድሜአቸውም አምሳ ዓመት ሲሞላ የአገልግሎታቸውን ሥራ ይተዋሉ፥ ከዚያም በኋላ አይሠሩም

25 And from the age of fifty years they shall cease waiting upon the service thereof, and shall serve no more:

26 የተሰጣቸውን ይጠብቁ ዘንድ ወንድሞቻቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለግላሉ የድንኳኑን አገልግሎት አይሠሩም። እንዲሁ ስለ ሥራቸው በሌዋውያን ላይ ታደርጋለህ።

26 But shall minister with their brethren in the tabernacle of the congregation, to keep the charge, and shall do no service. Thus shalt thou do unto the Levites touching their charge.